Local Bahir Dar Amhara news, Ethiopia
የኢትዮጵያ ስም አጠራር
እኛ በመስራቅ አፍሪካ የምንገኚ ህዝቦች ስለታሪካቺን አንዳንድ ሙሉ
ማስረጃ መሰጠት ብንቺም በተለይ ስለ ስማቺን አጠራር ግን የምናውቀው ነገር ምንም የለም። ሁሉም የውጭ ሀገር ሰወቺ የሰጡን ስም ነው።አብዛኛው የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሀፊወች የኢትዮጵያ ማለት ከግሪክ ቋንቋ የመጣ ነው ይላሉ ።
ፊቱ በጸሃይ የተቃጠረ ህዝብ ማለት ነው ብለው ይተረጉሙታል ሀበሻ ማለት ደግሞ ድብልቅ ህዝብ ነው ብለው ይተረጉሙታል ። የኢታሊያን ቅኚ ገጂወች ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረው በነበሩበት ጊዜ ከላይ የተጠቀሱ ሁለት ስሞቺንን ትተው ኢጣሊያቂ ምራባዊት አፍሪካ የሚል ስም ሰጥተውን በዚህ ስም በይፋ ስንጠራ ነበር።
ይህ ስም ኢርትራንነ ሱማሌን የሚያጠቃልል ነበር። ስለስማቺን አሰጣጥ በተመለት ከዚህ በታቺ አቀርባዋለሁ
1ኛ የኢትዮጵያ ታሪክ ሙሁር የሆኑት ኮንቲሮሊኒ በ 1937 ዓም በደረሰው መጺሀፍ የራሱን መንግስት ያወጣው ስም ኢጣሊያቂ ምራባዊት አፍሪካ የሚለውን አጠራር ወደ ጎን በመተውና በመቃወም ኢትዮጵያና ህዝቦቿ በተባለው መጺሀፉ ከ3 በላይ የተጠቀሱ ስሞች ኢትዮጵያ የሚለውን በመምረጥ ትክክለኛ ስማቺን መሆን እለበት ስለአመነበት አስፍሮታል። 1000 ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት ይኖር የነበረ ታዋቂው የታሪክና የግጥም ደራሲ ሆሜር ሀገራቺንን ኢትዮጵያን እያለ ገጥሞላታል። ከሱ በፊትም መጺሀፍ ቅዱስ ብሉኪዳን የኢትዮጵያ ስም ተጠቅሶ ይገኛል ። ስለዚህ ኢትዮጵያ የሚለው ስማችን ጥንታዊነቱ አያጠራጥርም ። ኮንቲ ሮሊኒ ከላይ በተጠቀሰው መጺሀፍ ሀበሻ ማለት በአረበኛ ቋናቋ ድብልቅ ህዝብ ከሚለው ቃለ የተወሰደ ነው የሚለው አባባለ ከእውነት የራቀ መሆኑን ሀበሻ ስማችን ከኢትዮጵያ ስማቺን በጥንታዊነት ቀደምትነት እንዳለው ኮንቲ ሮሲኒ ጠቅሶ የኢትዮጵያ የተለመደው ከክርስቶስ ልደትበኋላ ሲሆን ሀበሻ ግን ከክርስቶስ ልደት በፊት የምንጠራበት ነበር። ኢትዮጵያ የተከለለቺ ከተፈጥሮዊ ገጽታዋ አንድ ምድረ ገጽ አንድነት ያላትአገር ስትሆን ዋና አካሎ ግዙፍ የሆኑ ተራራማ ቦታወቿ ናቸው።እንደዝሁም ጥለቀት ባላቸው የመሬት ቁፋሮ የተከፋፈሉ ከፍተኛ ቦታወች ናቸው።የሰሜን የናይል ቆላማ ቦታ ቅጥያ ሲሆን እንደዝሁም በደቡብ በኩል ቆላማ ቦታ ያዋስናታል። ኢትዮጵያ በዘርዋ በኩል ዋናው የኩሽ ህዝብ ሃገር ተብላ ልትጠራ ትቺላለቺ። በሰሜን ከናይል ወንዝ በሰተምስራቅ እስከ መሃል አካሎ የሆነ አንድ ክፈል ብቻ ተቆርሶባታል። ይህ ማለት በሰሜን ሱዳን ከሰላ አውራጃ ማለት ነው ። ከደቡብ እና ከምስራቅ ከዘሮቿ አንድ ክፍል የሆነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቆርሶባት ይገኛል። ኬንያና ጂቡቲ። አቢሲኒያ ሲባል በደቡብ በኩል አዋሺን የሚያዋስናት ሲሆን ዘርና ቋንቋ የኩሽና የሴምን የወሰዱ ህዝቦች የሚኖሩባት ናት። ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ሲባል በተፈጥሮ ምድረ ገጽ እና የዘር ክልል የሚያመለክት ሲሆን አቢሲኒያ ሲባል ግን የአንድ ታሪካዊ ሂደት ወይም ወቅት የሚገልጽ ነው። የኢጣሊያ ቅኝ ገጂወች አውጥተውልን የነበረው 3ኛ ስም ግን በታሪክም ረገድ በቋንቋም ዘርፍ አጉል አጠራር ስለሆነ እንደ ኬንያ ኦጋንዳ ታንዛኒያ የመሳሰሉ በምስራቅ አፍሪካ ስላሉበወቅቱ የነበሩ ፋሺሽታውያን አገዛዝን ሳይፈራ ኮንቲ ሮሲኒ ውድቅ አድርጎታል።
ስለ ስማቺን ከፍተኛ ምርምር ያካሄደው ሰው ፈረንሳዊ ሻን ደረሰ ነው በ አፍሪካ ቀንድ የሚል አርእስት መጽሀፍት ከክርስቶስ ልደት በፊት 1500 አመት በጥንታዊ ግብጽ የተደረገው የባህር ጉዞ ባቲ ቤተ መቅደስ ተቀርጾ የሚገኘው ታሪካዊ ስእል በሚመረመርበት ጊዜ ነበር። የ5 መርከቦች ያቀፈ 350 ባህርተኞች ተካፍለውበት የነበረ ኮንቲ ሮሲኒ በአለም የመጀመሪያ ትልቅ የባህር ገጽታ (ጂኦግራፊ) ጉዞ ብሎ ሰይሞታል። ይህ ታሪካዊ ጉዞ ለማዘጋጀት ስሟን ታዋቂ ያደረገው አታሉ (ራማካ) ማካራ ተብላ የምትጠራ ንግስት ስትሆን እንደ ንግስት የራሶን ሀውልት እንድታሰራ በራሷ ስም ቤተመቅደስ እንድታሰራ በ 18ኛው ዲናስቲ የቱትሞሲስ 1ኛ ልጅ ነት።ይህ አጠራር ግን የሃባሻ ህዝብን የአክሱምን መንግስት ከመሰረቱት አንዱ ሲሆን የስድብ አጠራር አረበኛ ቋንቋ ድብልቅ የሚለው ምንም ግንኙነት የለውም በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ አቢሲኒያ ተብላ ትጠራለቺ ። በጥንትጊዜ አረቦች “ቀይ ባህር ባህር አል ሃባሻ “| ብለው ይጠሩት እንደነበር ኮንቲ ሮሲኒ ባወጣው የጥንት ጂኦግራፊ ካርታ ያስረዳል በዚህም መሰረት ንጉስ ኢዛና የ አቢሲኒያ ንጉስ ተብሎ ነበር ይጠራ የነበረው ።
ቦታም በሚመለከት በቶካር ለምሀር አካባቢ መሆን እንዳለበት ብሎ ደምድሟል። ጆንጆሬስ የግብጽ መርከቦች የንግድ
መሆናቸውም ከአመለከተ በኋላ ለወረራና ለዘረፋ የሚውል የጦር መሳሪያ እንዳልጫኑ የሚሄዱበት ሀገርም ንግድ በደላማዊ መንገድ የሚካሄድበት ሰላም ወዳድ መሆናቸውን ሀገሩንም የእግዚሃብሄር ሀገር ተብሎ የሚጠራ ቅዱስ ሀገር መሆኑን የሁለት ሀገሮች (ግብጽና ቱርክ) የጋራ እግዚሃብሄር በአሞን የሚያምኑ መሆናቸውን ይገልጻል። ባህርተኞች ያረፉበት ቦታም በኤደን ባህረ ሰላጤ አካባቢ በሆን እንዳለበት ገምቷል። ስለዚህ ዘረፋ ሊካሄድ እንደማይችል ይገመታል።
ወሳኝ ኩነቶች እና የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ
I. አጠቃለይ ዓላማ
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርዓት ግንባታ ሂደት ወደ ላይ፣ ወደታች እንዲሁም ወደ ጐን ተቋማዊና ሙያዊ ግንኙነት እና ትስስር በመፍጠር ዘላቂነት ባላው ግንዛቤ ፈጠራ፣ ድጋፍና ትብብር ሕጋዊ፣ አስተዳደራዊና ስታትስቲክስ መረጃዎችን የሚያስገኝ የተቀናጀ የመረጃ ስርዓት ነው፡፡ ይሁን እንጅ በዓለም ብሎም በሀገራች በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽ በሽታ ምክንያት የአካል ድጋፍም የፊት ለፊት ስልጠናዎችን መስተት አልተቻለም፡፡ በመሆኑም ሚዲያ የሚከታተለውን የህብርተሰብ ክፍል በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ጽንሰ-ሐሳብ፣ አስፈላጊነት እና ጠቀሜታ በማስገንዘብ በበሽታው ምክንያት ሳይዘናጉ የሚከሰቱ ኩነቶችን በራስ ተነሳሽነት እንዲያስመዘግቡ ማስቻል የዚህ ሰነድ አጠቃላይ ዓላማ ነው፡፡
II. የሰነዱ አጭር መግለጫ
በዚህ ሰነድ ውስጥ ስለ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ጽንሰ-ሐሳብ፣ ስለ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አስፈላጊነት እና ጠቀሜታን፣ እያንዳንዱን ኩነት አስመዝጋቢና ከአስመዝጋቢዎች የሚጠበቁማስረጃዎችን የሚመለከቱ ጉዳዮች በዝርዝር ቀርበዋል፡፡
III. የሚጠበቅ ዉጤት
ሚዲያ የሚከታተለው የህብርተሰብ ክፍል በዚህ ሰነድ ላይ ተመስርቶ የሚሰጠዉን የግንዛቤ ማስጨበጫ በሚገባ በመከታተል የወሳኝ ኩነት እና የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ምንነት፣ ስለ ወሳኝ ኩነቶች አይነቶችና መገለጫቸው እንዲሁም መርሆዎች፣ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ተገንዝበዉ የሚከሰቱ ኩነቶችን በማስመዝገብ በሀገራችን የተዘራውን የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስርዓት በመገንባት ረገድ የበኩላቸውን ሚናቸዉን ይወጣሉ፡፡
ክፍል አንድ:- ወሳኝ ኩነቶች እና የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ
1.1. የወሳኝ ኩነት ምንነት
የወሳኝ ኩነትን ምንነት ከሦስት አተያዮች ላይ ተመስርተን እንመለከታለን፡፡ እነዚህም የመዝገበ ቃላት ትርጉም፣ በሀገራችን የወሳኝ ኩነቶችን ምዘገባ ስርዓት ለማስተግበር በወጡ ህጎች የሰጠ ትርጉም እና በተባባሩት መንግስታት ድርጅት የተሰጠዉ ትርጉም ፡፡
1. የመዝገበ ቃላት ትርጉም፡- ወሳኝ ኩነት የሚለው ወሳኝ እና ኩነት ከሚሉ ሁለት ቃሎች የተገበና ሲሆን፡
ወሳኝ (Vital) ማለት፡- በጣም አስፈላጊ፣ እጅግ አስፈላጊ (English Amharic Context Dictionary, Wolf Leslau, 1973) ማለት ሲሆን፡
ኩነት (Event) ማለት ደግሞ ተፈጸመ፣ ተደረገ፣ ተከናዎነ፣ ወይም አንድ አይነት መጠን፣ መልክ፣ ባህርይ፣ ግብር፣ ስራ ያዘ (የአማርኛ መዝገበ ቃላት የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ምርመር ማዕከል፣ በ1993ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ)፡፡ ስለዚህ ወሳኝ ኩነት ማለት በጣም አስፈላጊ ድርጊት ፣ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ማለት ነዉ፡፡
2. በተባበሩት መንግስታት ድርጅት፡- ወሳኝ ኩነቶች በመባል ሚታወቁት በህይወት መወለድ (Live Birth)፣ የሽል ሞት (Feotal Death)፣ ሞት (Death)፣ ጋብቻ (Marriage)፣ ፍቺ (Divorce)፣ ጋብቻ እንዳልተከናወነ መቁጠር(Annulment)፣ ባልና ሚስትን ለጊዜው በህግ መለያየት (Legal Separation)፣ ጉዲፈቻ (Adoption)፣ በህጋዊ ጋብቻ ውስጥ ያልተወለደን ልጅ አባትነት ወይም እናትነት መቀበል (Recognition or judicial declaration of paternity) እና ልጅነትን መቀበል (Acknowledgement) ናቸዉ፡፡
3. የህግ ትርጉም፡- በሀገራችን የወሳኝ ኩነቶችን ምዘገባ ስርዓት ለማስተግበር በወጣዉ አዋጅ ቁጥር 760/2004 አንቀጽ 2(1) እና የክልሉን ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲን ለማቋቋም በወጣዉ ደንብ ቁጥር 120/2006 አንቀጽ 2(2) መሰረት “ወሳኝ ኩነት” ማለት ልደት፣ ጋብቻ፣ ፍቺ ወይም ሞት ሲሆን ጉዲፈቻን፣ ልጅነትን መቀበል እና አባትነትን በፍርድ ቤት ማወቅን ይጨምራል፤ በሚል ተተርጉሟል፡፡
ለእያንዳንዳቸው ወሳኝ ኩነቶች የተሰጠው ትርጉም ከዚህ በታች በአጭሩ ቀርቧል፡፡ እነዚህ ትርጓሜዎች የምዝገባውን የሕግ፣ የአስተዳደርና የስታትስቲክስ ዓላማ በጥምረት እንዲያሳኩ ታልመው የተዘጋጁ ሲሆን ሀገሮችም የምዝገባና ስታትስቲክስ ስርዓቱን በማቋቋምና በማካሄድ የአሰራር መርህ አድርገው እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ (ተ.መ.ድ 2014፡ (3-4))፡፡
1. በሕይወት መወለድ /Live Birth/፡- ልጅ በሕይወት ተወለደ የሚባለው የእርግዝናው ጊዜ ከግምት ውስጥ ሳይገባ ሕፃኑ ከእናቱ ማህጸን እንደወጣ ወዲያውኑ ሕይወት ያለው መሆኑ ከታወቀ ነው፡፡ ሕጻኑ ሕይወት ያለው መሆኑ የሚታወቀው ጽንሱ በማህጸን የቆየበት ወራት ከግምት ውስጥ ሳይገባ ከእናቱ ማህጸን በሚወጣበት ወቅት የሚተነፍስ ከሆነ ወይም እትብቱ ከመቆረጡ በፊት ወይም ከተቆረጠ በኋላ ሌላ በሕይወት የመኖር ምልክት/ለምሳሌ የልብ ትርታ፣ የጡንቻዎች እንቅስቃሴ/ካሳየ ነው፡፡ ተ.መ.ድ (2ዐ14፡3)
2. ሞት /Death/፡- ሞት ተከሰተ የሚባለው አንድ በሕይወት ይኖር የነበረ ሰው ወይም በሕይወት የተወለደ ሕጻን በበሽታ፣ በአደጋ ወይም ተለይቶ ባልታወቀ ምክንያት በሕይወት ያለ መሆኑን የሚያሳውቁ ምልክቶች ሙሉ ለሙሉ ለዘለቄታው ሲለቁትና እንደገና ነፍስ ለመዝራት የማይችል መሆኑ ሲረጋገጥ ነው፡፡
3. የሽል ሞት /Foetal Death/፡- የሽል ሞት ተከሰተ የሚባለው የእርግዝና ጊዜ ከግምት ውስጥ ሳይገባ ሕፃኑ ከእናቱ ማህጸን ሳይወጣ ሙሉ ለሙሉ የሞተ እንደሆነ ወይም ከእናቱ ማህጸን ከወጣ በኋላ ሕይወት ያለው መሆኑን የሚያሳውቁ ምልክቶች ማለትም የመተንፈስ፣ የልብ ትርታ፣ የጡንቻዎች እንቅስቃሴ ካልታዩ ነው፡፡ ይህ ትርጓሜ ሰፊና እርግዝናው ሕይወት ያለው ሕፃን ያላስገኘን ክስተት በመሉ የሚመለከት ነው፡፡
4. ጋብቻ (Marriage)፡- እንደ የአገራቱ ህጎች ዕድሜያቸው ለጋብቻ የደረሱ አንድ ወንድና አንዲት ሴት በህጋዊ መንገድ ለዘለቄታው አብሮ በመኖር ሃሣብ በራሳቸው ነፃ ምርጫ ፈቅደው በይፋ የሚመሠርቱት ግንኙነት ወይም በዚሁ ግንኙነታቸው አማካኝነት የሚዋቀር ሕጋዊ ተቋም ነው፡፡ የጋብቻ ህጋዊነት የሚረጋገጠው በሲቪል ህግ፣ በሃይማኖት ወይም በአገራት ህግ ዕውቅና በተሰጣቸው ሌሎች ባህላዊ አሰራሮች ነው፡፡
5. ፍቺ /Divorce/፡- ፍቺ ማለት በሕጋዊ መንገድ ተመስርቶ የነበረ ጋብቻ ሙሉ ለሙሉ ህጋዊ በሆነ መንገድ በሀገሩ ሕግ መሰረት ሲፈርስና ሁለቱም ለጋብቻ መፈጸም የሚያስችላቸውን መብት የሚያገኙ መሆናቸው ሲረጋገጥ ነው፡፡
6. ጋብቻ እንዳልተከናወነ መቁጠር /Annulment/፡- የየሀገሩን የፍታሐ-ብሄር ሕግ መሰረት በማድረግ ስልጣን በተሰጠው አካል ጋብቻ እንዳልተፈጸመ ወይም ጋብቻውን በመሰረዝ ተጋቢዎች ከዚህ በፊት ጭራሽ ተጋብተው እንዳልነበረ መቁጠርን ይመለከታል፡፡
7. በህግ መለያየት /Legal separation/፡- የየሀገሩ የፍትሐብሄር ሕግ መሰረት
በማድረግ ተጋብተው የነበሩ ግለሰቦችን ማለያየት፣ ሆኖም እንደገና የማግባት መብት ያለመስጠትን ይመለከታል፡፡
8. ጉዲፈቻ/Adoption/፡- ማለት የየሀገሩን የፍትሐ-ብሄር ሕግ መሰረት በማድረግ የራስ ያልሆነን ልጅ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት በፀደቀ ስምምነት የራስ ልጅ ማድረግ ነው፡፡
9. ልጅነትን መቀበል /Legitimation/፡- ከጋብቻ ውጭ የተወለደን ግለሰብ በህጋዊ ጋብቻ ውስጥከተወለዱት ዕኩል ደረጃና መብት መስጠትን ይመለከታል፡፡ አንድ ሰው አንድን የተወለደ ልጅ የእርሱ ልጅ መሆኑን አግባብ ባለው ህግ መሰረት አምኖ ቃሉን ሲሰጥ ነው፡፡
10.አባትነትን በፍርድ ቤት ማወቅ / Recognition /፡- የልጅ አባት ያልታወቀ ወይም የተካደ ከሆነ የልጁ አባት ማን እንደሆነ በፍርድ ቤት ውሳኔ ሲረጋገጥ ነው፡፡
ወሳኝ ኩነቶች ሲባል አንድ ሰው ወደ ህይወት የሚገባበትና በህይወት ዘመኑ ውስጥ የሚያልፍባቸው ወሳኝ ተፈጥሮአዊና ማህበረሰባዊ ክስተቶች ናቸው፡፡
ü ተፈጥሯዊ ኩነቶች የሚባሉት፡- ልደት፣ ሞትና የሽል ሞት ሲሆኑ፣
ü ማህበረሰባዊ ኩነቶች የሚባሉት፡- ቀሪዎቹ 7 ኩነቶች ናቸው ፡፡
Ø ከሚሰጣቸው ትኩረት አንፃር ኩነቶች በሦስት ይከፈላሉ። እነዚህም፡-
- ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጣቸው /first priority/ ኩነቶች፡- ልደትና ሞት፣
- መካከለኛ ትኩረት የሚሰጣቸው /second priority/ ኩነቶች፡- ጋብቻ፣ ፍቺና የሽል ሞት፣
- ዝቅተኛ ትኩረት የሚሰጣቸው/low priority/ ኩነቶች ቀሪዎቹ 5ቱ ናቸው ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርዓትን በአንድ ሀገር ለማደራጀት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ኩነቶች ልደት፣ ሞት፣ ጋብቻና ፍቺ እንደሆኑ ይገልጻል፡፡
ልደትና ሞት በሰው ልጅ ላይ አንድ ጊዜ የሚከሰቱ ተፈጥሮአዊ ክስተቶች ናቸው፡፡ ሰዎች በልደት አማካይነት ወደ ዓለም ህብረተሰብ ይቀላቀላሉ፤ በአንጻሩ በሞት አማካይነት ከዓለም ይለያሉ፡፡ ልደትና ሞት በሰው ልጅ አፈጣጠርና አኗኗር የህይወት መነሻና መድረሻ እርከኖች መለያ ናቸው፡፡ የልደት ኩነት በዚህ ምድር የሰዎች የመኖር ህጋዊ መብት ምንጭ በመሆኑ ማንኛውም ሰው በአንድ በታወቀ የአስተዳደር ክልል ለመኖር ህጋዊ የዜግነትና ማንነት መብት የሚያገኝበትና ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነውን ህጋዊ ሰነድ በመንግስት የሚዘጋጅበት የህይወቱ የመብት መነሻ እርከን ነው፡፡ በአንጻሩ ሞት የዚህ መብት መጨረሻ ወይም መቆሚያ እርከን ነው፡፡
ጋብቻና ፍቺ ሰው “ህጋዊ ሰው” የመሆን መብት በሚያገኝበትና በሚያጣበት የማህበረሰባዊ አኗኗር ስርዓት ውስጥ የሚከሰቱ ዋነኛ የሰዎች ማህበረሰባዊና ህጋዊ አቋም ለውጥ ጠቋሚ ኩነቶች ናቸው፡፡ እነዚህ በግለሰቦች ላይ የሚከሰቱ ተፈጥሮአዊና ማህበረሰባዊ ለውጦች የአንድን ሀገር የህዝብ አስተዳደር በስርዓት ለመምራት መነሻ መሰረቶች ናቸው፡፡
1.2. የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ (civil registration)
የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ማለት በአንድ ሀገር ክልል ውስጥ የሀገሪቱ ህግ በሚፈቅደው መሰረት በተቋቋመ ተቋም የወሳኝ ኩነቶችን መከስትና ባህሪያት ተከትሎ ተከታታይ፣ ቋሚና፣ አስገዳጅ በሆነ መንገድ ምዝገባ ማካሄድ ሲሆን፣ የአንድን ግለሰብ ማንነት የሚገልጹ ሕጋዊና ግለሰባዊ ማስረጃዎችን በማስገኘት ዓላማ ላይ የተመሰረተ ነዉ፡፡ ግለሰቦች ከልደት እስከ ሞት ድረስ በግላቸውና በማህበረሰብ አባልነታቸው የሚከሰቱባቸዉን ኩነቶች እና ከእነዚህ ኩነቶች ጋር ተዛማጅ የሆኑ የሥነ-ሕዝብ፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ባህሪያት ያካተቱ መረጃዎችን ለምዝገባዉ ተግባር ሲባል በወጣው አስገዳጅ ሕግ መሰረት በተከታታይነት እና በቋሚነት የመመዝገብ፣ ለግለሰቦች የምስክር ወረቀት የመስጠትና መረጃውን የመጠበቅ እንዲሁም ለወሳኝ ኩነቶች ስታቲስቲካዊ መረጃ አሰባሰብና ጥንቅር ግብዓት የሚሆኑ ግለሰባዊ መረጃዎችን የመሰብሰብ ተግባራትን የሚያጠቃልል የመረጃ አሰባሰብ ዘርፍ ነው፡፡
1.3.የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስርዓት (civil registration
system)
በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ተግባር ላይ በመመስረት አስፈላጊውን ህጋዊ አስተዳደራዊና ተቋማዊ አወቃቀር የመዘርጋትና ለህጋዊ፣ ለአስተዳደራዊና ስታትስቲካዊ ጠቀሜታዎች ግብዓት የሚሆኑ አስፈላጊ ግለሰባዊ መረጃዎችን አግባብ ባለው ቴክኒካዊ አሰራር የማመንጨትና አደራጅቶ የመያዝ ስራ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስርዓት (civil registration system) በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ስርዓት በአንድ ሀገር የሚከሰቱ ወሳኝ ኩነቶች ደረጃውን በጠበቀ፣ በተቀናጀና አግባብ ባለው ቴክኒካዊ አሰራር ለመመዝገብ የሚያስችሉ ተቋማዊ እና ሕጋዊ አደረጃጀቶችን ከሀገሪቱ የማህበራዊና ባህላዊ ሁኔታዎች ጋር በተገናዘበ መልኩ በማደራጀት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አሰራርን በመላ ሀገሪቱ እውን የማድረግ ተግበራትን የሚያጠቃልል የምዝገባ ስርዓት ነው፡፡
1.4.የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ሥርዓት መሠረታዊ የአሠራር መርሆዎች
አንድ አገር የወሳኝ ኩነትን ምዝገባ ስርዓት ለመዘርጋት/ተግባራዊ ለማድረግ የሚከተሉትን የአሰራር መርሆች ተፈጻሚ ማድረግ እንዳለባችዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይገልጻል፡፡
1. አንድ ኩነት ከተከሰተ በአጭር ጊዜ ውስጥ መመዝገብ ይገባዋል፡- የኩነቶች ምዝገባ የጊዜ ገደብ በሶስት የምዝገባ የጊዜ ገደብ በመከፈል በህጉ ሊደነገግ ይገባል፤ እነርሱም መደበኛ ወይም ህጋዊ የምዝገባ ጊዜ፣ የዘገየ የምዝገባ ጊዜ እና ጊዜ ገደቡ ያለፈ ምዝገባ ጊዜ በመባል ይለያሉ፡፡ በተቻለ መጠን የተከሰቱ ኩነቶች በመደበኛዉ የምዝገባ ጊዜ መመዝገብ ይኖርባቸዋል፡፡
2. ሁሉንም የተከሰቱ ኩነቶች መመዝገብ አለባቸዉ፡- የተከሰቱ ሁሉም ኩነቶች በምዝገባው መሸፈን ይገባቸዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአንድ ወሳኝ ኩነት የምዝገባ ሽፋን የተሟላ ነው የሚባለው በአገሪቱ በዓመቱ ከተከሰቱ ኩነቶች ከ90 በመቶ በላይ በምዝገባው መሸፈን ከቻሉ ነው፡፡
3. ሁሉንም ኩነቶች የማቀፍ አቅጣጫን የመከተል፡- በምዝገባ አዋጁ የተመለከቱት ሁሉም ወሳኝ ኩነቶች (ልደት፣ ሞት፣ ጋብቻና ፍቺ) እና ተከታይ ወይም ተዛማጅ ኩነቶች (ጉዲፈቻና አባትነትን በህግ መቀበል) የቀበሌ አስተዳደር ጽ/ቤቱ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ሥርዓት አካል ሆነው ይከናወናሉ፡፡
4. ምዝገባው ሁሉንም የአስተዳደር አካባቢዎችና ማህበረሰቦች መሸፈን ይገባዋል፡-የኩነቶች ምዝገባ አገር አቀፍ የመረጃ ፍላጎትን ለማሟላትና ሁሉን አቀፍ ለመሆን ምንም ቦታዎችንና ቤተሰቦችን ሳይለይ/ሳይዘል በሁሉም አካባቢዎች ሊካሄድ ግድ ይላል፡፡
5. ምዝገባው መቋረጥ የለበትም፡- ኩነቶች ያለማቋረጥ የሚከሰቱና የሚከናወኑ ተፈጥሯዊና ማህበራዊ ክስተቶች በመሆናቸው የኩነቶች ምዝገባ አንዴ ከተጀመረ ለቀናትም ቢሆን ሊቋረጥ የማይገባዉ ተግባር ነዉ፡፡
6. ምዝገባው በቋሚነት በተቋቋመ የመንግስት ተቋም መከናወን ይገባዋል፡- የኩነቶች ምዝገባ በህግ በቋሚነት በተቋቋሙ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች ሀላፊነት ሊከናወን ይገባል፡፡ የአገልግሎት አደረጃጀትና አሠራርም ቋሚነትን ሊያመጣ በሚያስችል መልኩ መደራጀት ይገባዋል፡
7. ምዝገባው በህግ መደገፍ ይኖርበታል፡- የኩነቶች ምዝገባ መረጃዎች በቀዳሚነት የሚፈለጉት ህጋዊ ለሆኑ ግለሰባዊና የመንግስት አስተዳደራዊ እና ማህበራዊ አገልግሎቶች ነው፡፡ የሚመዘገቡት መረጃዎችም ሆኑ የሚዘጋጁት ማስረጃዎች አስቀድሞ ህጋዊ መስፈርት ማሟላታቸውን የሚያረጋግጥ አሠራር መነደፉ መረጋገጥ ይገባዋል፡፡
8. የምዝገባው ተቋም ለህብረተሰቡ ቅርብ በሆነ ቦታ ሊደራጅ ይገባል፡- የኩነቶች ምዝገባ አደረጃጀትና አሠራር ከማዕከል ጀምሮ የሚከናወን ቢሆንም የምዝገባውን ሥራ የሚያከናውነው የአካባቢ የምዝገባ አገልግሎት ጽ/ቤት ህብረተሰቡ በቅርበት ሊገለገልበት በሚችልበት አስተዳደር ዕርከን መቋቋም እንዳለበት በህግ መደንገግ ይኖርበታል፡፡
9. ምዝገባው ለባለመብቶች የኩነት ምስክር ወረቀት መስጠት ይገባዋል፡- የኩነቶች ምዝገባ እንደተፈጸመ በአጭር ጊዜ ውስጥ የምስክር ወረቀት ተዘጋጅቶ ለባለጉዳዩ መሰጠት ይገባዋል፡፡ ስለሆነም የምዝገባው አሠራር የምስክር ወረቀት ዝግጅትና ምስክር ወረቀት የመስጠት አገልግሎት ማጣመር ይኖርበታል፡፡
10. ህብረተሰቡ ስለምዝገባው ተከታታይና ቋሚ ትምህርት ሊሰጠው ይገባል፡- ከላይ እንደተገለጸው አንድ ኩነት በተከሰተ አጭር ጊዜ ውስጥ መመዝገብ ይገባዋል፤ ይህ ሊሆን የሚችለው ግለሰቦች፣ ቤተሰቦችና ህብረተሰቡ ስለምዝገባው ጥቅምና አስፈላጊነት ተረድተው በራሳቸው ተነሳሽነት ኩነቱን እንደተከሰተ ወይም በህግ በተደነገገዉ ጊዜ ዉስጥ የማስመዝገብ ባህል ሲያዳብሩ ነው፡፡ ለዚህም በድርጊት መርሀ-ግብር የተደገፈ ተከታታይና ቋሚ የትምህርት ፕሮግራም ማዘጋጀት ይገባል፡፡
1.5.የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ መረጃ ባህሪያት
1. ተከታታይነት /continuity /፡- በህዝብና ቤቶች ቆጠራ እንዲሁም በናሙና ጥናት ከሚሰበሰቡ የዜጎች የሥነ ህዝብ መረጃ ይልቅ ከወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርዓት የሚገኙ መረጃዎች ቀጣይነትና ተከታታይነት ባለው መንገድ የሚሰበሰቡ መሆናቸው፤ ማለትም የሚካሄደው የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ በምንም ሁኔታ የማይቋረጥ መሆኑ፣
2. ወጥ እና ተነጻጻሪ /consistency & comparability/፡- በወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሥርዓት የሚሰበሰቡ የወሳኝ ኩነት መረጃዎች በዓለም አቀፍ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስታንዳርድ ላይ ተመስርተው የሚሰበሰቡ በመሆናቸው በየጊዜው የማይለዋወጡ፣ ወጥነት ያላቸው እና አንዱን አካባቢ ከሌላው አካባቢ ጋር ለማነፃፀር የሚያስችሉ መሆናቸው፣
3. የተሟላ /Completeness/፡- በአግባባዊው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሥርዓት ሁሉንም ኩነቶች፣ የህብረተሰብ ክፍል እና አከባቢ ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ የምዝገባውን አገልግሎት ተደራሽ የሚያደርግ ሥርዓት በመሆኑ እንዲሁም መረጃዎቹ የሚሰበሰቡት ቀጥታ ከምንጩ በመሆኑ የወሳኝ ኩነት መረጃዎች የተሟሉ መሆናቸው፣
4. ትክክለኛነት/correctness/፡- በወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሥርዓት የሚመዘገቡ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ መረጃዎች በመደበኛ የጊዜ ሰሌዳ እና በቅርበት የሚመዘገቡ በመሆናቸው ከሌሎች የወሳኝ ኩነት መረጃ ማለትም ሕዝብና ቤቶች ቆጠራ እና የናሙና ጥናት የስነ ህዝብ መረጃ ማሰባሰቢያ መንገዶች በተሻለ ትክክለኛ የወሳኝ ኩነት መረጃ ማስገኘት የሚያስችል በመሆኑ፣
5. በህግ ፊት በራሱ በቂ የሆነ ማስረጃ (authenticity) - በቀበሌ አስተዳደር ጽ/ቤት ደረጃ የሚተገበረው የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ተግባር የሚያዘጋጃቸው እያንዳንዳቸው የኩነት ማስረጃዎች /የኩነት ምስክር ወረቀት/ በህግ ፊት ወይም በፍርድ ቤቶች ሲቀርቡ በራሳቸው ያለተጨማሪ ማስረጃ በቂ መሆናቸው፡፡
6. ጠቃሚነት/utility/ - የወሳኝ ኩነት ምዝገባ መደበኛ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ አሰራር ተከትሎ የሚከናወን በመሆኑ ለፖለቲካዊ፣ ለማህበራዊ እና ለኢኮኖሚያዊ ዕቅዶች ቋሚና አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ በመሆኑ፣
7. ተቋማዊ ዘርፈ-ብዙነት ያለው /multi-Sectoral/ - ከተለያዩ ተቋማት ጋር ግንኙነት ያለው፤ የተለያዩ ሴክተሮችን ቅንጅታዊ ተሳትፎ የሚጠይቅና እንዲሁም የሚያስገኘው መረጃ ለተለያዩ ተቋማት ዕቅድ ዝግጅትና ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ ለመንደፍ ግብዓት ሆኖ የሚያገለግል የተቀናጀ ዘመናዊ የመረጃ ስርዓት መሆኑ፣
8. ሙያዊ ዘርፈ -ብዙነት ያለው /multi-desciplinary/ - የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሥርዓት ግንባታና ትግበራ የተለያዩ የሙያ መስኮችን ጥምረት የያዘና ሙያዊ ድጋፍ የሚጠይቅ መሆኑ::
1.6. የወሳኝ ኩነቶች የምዝገባ ጊዜ
አገራት እንደየራሳቸዉ ነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ማለትም የፖለቲካ ስርዓት እና አደረጃጀት፣ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስርዓት ተቋማዊ አደረጃጀት መዋቅር፣ ባህልና ልምድ፣ የቴክኖሎጅ አጠቃቀም እና የመንገዶች ተደራሽነት መሰረት ኩነቶች ከተከሰቱ በስንት ጊዜ ዉስጥ መመዝገብ እንዳለባቸዉ ስርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያወጡት ህግ ወስነዉ ያስቀምጣሉ፡፡ የአንዳንድ አገሮችን የምዝገባ ጊዜ ለተሞክሮ ስናይ፡
ህንድ፡- የልደት እና የሞት ኩነቶች ከተከሰቱ እስከ 21ኛዉ ቀን መመዝገብ አንዳለባቸዉ፣ሲዘገዩ ደግሞ ከ22ኛዉ እስከ 30ኛዉ ቀን እና ወቅቱ ያለፈበት ምዝገባ የሚባለዉ ከ30ኛዉ ቀን በኋላ እንደ ሆነ፡፡
ግብፅ፡- ልደት፣ጋብቻ እና ፍች ከተከሰቱ እስከ 15ኛዉ ቀን ሲሆን ሞት እና የሽል ሞት በ24 ስዓት ዉስጥ መመዝገብ እንዳለባቸዉ በህጋቸዉ አስቀምጠዋል፣
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሶስት ዓይነት የወሳኝ ኩነቶች የምዝገባ ጊዜ አሉ ፡፡ እነዚህም
1. ወቅቱን የጠበቀ ምዝገባ (current registration):-
በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ እና የብሔራዊ መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 760/2004 መሰረት ወቅታዊ ምዝገባ የሚባለዉ ልደት ከሆነ ልደቱ በተከሰተ ባሉት 90 ቀናት እና ሌሎች ኩነቶች ደግሞ ኩነቶች በተከሰቱ በ30 ቀኖች ውስጥ መመዝገብ ሲችሉ እንደሆነ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በዚህ አዋጅ በተደነገገው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያልተፈፀመ እንደሆነ አስመዝጋቢው የዘገየበትን ምክንያት በማስረጃ ማስደገፍ አለበት፡፡ ህጉ/አዋጁ ማንኛዉም ኩነት የተከሰተበት/የተፈጠረለት ግለሰብ ኩነቱን በወቅቱ ከላስመዘገበ በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከአምስት መቶ ብር እስከ አምስት ሺ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚቀጣ በአንቀጽ 66(1)(ሀ) በግልጽ አስቀምጧል፡፡
2. የዘገየ ምዝገባ ( late registration)
በሀገራችን የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስርዓት ለመዘርጋት የወጣዉን አዋጅ (በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ እና የብሔራዊ መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 760/2004) ለማስፈጸም/ለማስተግበር በወጣዉ መመሪያ መሰረት የዘገየ ምዝገባ የሚባለዉ ልደት ኩነቱ ከተከሰተ ከ91ኛዉ ቀን ፣ሌሎች ኩነቶች ደግሞ ከ31ኛዉ ቀን ጀምሮ እስከ 365ኛዉ ቀን (አንድ ዓመት) ድረስ መመዝገብ ሲችሉ እንደሆነ በግልጽ ተደግጎ ይገኛል፡፡
3. ጊዜ ገደቡ ያለፈበት ምዝገባ (delayed registration)
ይህ የምዝገባ ጊዜ ኩነቱ ከተከሰተ ከ365ኛዉ ቀን (ከአንድ ዓመት) በኋላ የሚመዘገብ ምዝገባ ነዉ፡፡ ጊዜ ገደቡ ያለፈበት የኩነት ምዝገባ የወሳኝ ኩነቶች ምዝባ ከሚያስገኘዉ ህጋዊ ፣ አስተዳድራዊ እና ስታትስቲካዊ ጠቀሜታዎች ዉስጥ ለስታትሰቲክሳዊ ጠቀሜታ አይዉልም፡፡ ይሁን እንጅ ጊዜ ገደቡ ያለፈበት የኩነት ምዝገባ ካለዉ ከፍተኛ ግለሰባዊ ጠቀሜታ አንጻር በሀገራችን ተገባራዊ እየሆነ ባለዉ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስርዓት እንዲስተናገድ ተደርጓል፡፡
1.7. የወሳኝ ኩነቶች የምዝገባ ቦታ
ሁለት ዓይነት የወሳኝ ኩነቶች የምዝገባ ቦታዎች አሉ፡፡ እነዚህም
1. ኩነቶችን በተከሰቱበት ቦታ መመዝገብ (Registration by Place of Occurrence)
የሰዉ ልጆች በተለያዩ ምክንያቶች በጊዜያዊነትም ይሁን ለዘለቂታዉ ለመኖር በመደበኛነት ይኖሩበት ከነበረዉ ቦታቸዉ ለቀዉ ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ፡፡ ኩነቶች ደግሞ አንድ ሰው ወደ ህይወት የሚገባበትና በህይወት ዘመኑ ውስጥ የሚያልፍባቸው ተፈጥሮአዊና ማህበረሰባዊ ክስተቶች በመሆናቸዉ ሰዎች በእያሉበት ቦታ ሁሉ ይከሰታሉ፡፡ እነዚህን በእንቅስቃሴ ላይ ባሉ ሰዎች የተፈጠሩ ኩነቶችን ለመመዝገብ ሰዎቹ ወደ መደበኛ መኖሪያ ቦታቸዉ መመለስ ሳይኖርባቸዉ ኩነቱ በተፈጠረበት አካባቢ በሚገኝ የምዝገባ ጽ/ቤት የመመዝገብ ሂደት ኩነቶች በተፈጠሩበት ቦታ ምዝገባ (Registration by place of occurrence) ይባላል፡፡ ኩነቶችን በተከሰቱበት ቦታ ከሚመዘግቡ አገሮች ዉስጥ ህንድን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
2. በመደበኛ መኖሪያ ቦታ መመዝገብ (Registration by Place of Residence)
ይህ አመዘጋገብ ኩነቶች የትም ቦታ ይከሰቱ ወይም ይፈጠሩ ምዝገባዉ የሚካሄደዉ የኩነቱ ባለቤቶች (ኩነቱ የተከሰተላቸዉ ግለሰቦች) በመደበኛነት በሚኖሩበት አካባቢ በሚገኝ የምዝገባ ጽ/ቤት ይሆናል፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ የወሳኝ ኩነቶችን ምዝገባ ስርዓት ለመዘርጋት በወጣዉ ህግ ማለትም በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ እና የብሔራዊ መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 760/2004 መሰረት የኩነቶች ምዝገባ ሚካሄደዉ የኩነቱ ባለቤቶች በመደበኛነት በሚኖሩበት ቦታ እና በተለየ ሁኔታ አንዳንድ ኩነቶች ከመደበኛ መኖሪያ ቦታ ዉጭ እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ይህ ማለት አንድ የትዉልድ ቦታዉ ጎንደር ከተማ የሆነ እና በመደበኛነት እየሰራ የሚኖርበት ቦታ ደግሞ ባህርዳር ከተማ የሆነ ሰው ልደቱን አስመዝገቦ የልደት የምስክር ወረቀት ማዉጣት ቢፈልግ ወደ ትዉልድ ቦታዉ ጎንደር መሄድ ሳይጠበቅበት ባህር ዳር በሚኖርበት ቀበሌ በሚገኝ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ጽ/ቤት የኗሪነት መታወቂያ ይዞ በመሄድ የልደት ምስክር ወረቀት ማዉጣት ይችላል፡፡
1.8. የወሳኝ ኩነቶች የምዝገባ ስልቶች
የተለያዩ ሀገሮች ልምድ እንደሚያሳየዉ የወሳኝ ኩነቶች የአመዘጋግብ ስልቶች እንደየ ሀገራቱ የተለያዩ ናቸዉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በስልክ ተቀብሎ መመዝገብ፣ ቤት ለቤት ተንቀሳቅሶ መመዝገብ (active registration)፣ በአንድ ማዕከል ሆኖ መመዝገብ (Passive Registration) እንደ ምሳሌ ይጠቀሳሉ፡፡ ይሁንጅ እያንዳዱ ሀገር የሚጠቀሙትን የምዝገባ ስልት ስርዓቱን ለመዘርጋት በሚያዉጡት ህግ ወስነዉ ያስቀምጣሉ፡፡ ሁለቱን ስልቶች ምንነት እንደሚከተለዉ ለማብራራት ተሞክሯል፡፡
1. በምዝገባ ጽ/ቤት ሆኖ ኩነቶችን የመመዝገብ (Passive Registration) ስልት
በዚህ የምዝገባ ስልት መዝጋቢው (የክብር መዝገብ ሹሙ) ከምዝገባው ጽ/ቤት ሳይንቀሳቀስ ወሳኝ ኩነቱ ከተከሰተበት ቤተሰብ አባላት መካከል ወይም ኩነቱን የማስመዝገብ በሕግ ኃላፊነት የተጣለበት ሌላ ግለሰብ ወይም አካል ኩነቱ እንደተከሰተ በአቅራቢያው ወደሚገኘው የምዝገባ ጽ/ቤት በመሄድ ኩነቱንና ተዛማጅ የሆኑ የሥነ-ሕዝብ፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መረጃዎችን የሚያስመዘግብበት የአመዘጋገብ ስልት ነው። በዚህ የአመዘጋገብ ስልት የክብር መዝገብ ሹሙ የኩነቶችን ምዝገባ ከማከናወን ጎን ለጎን ጽ/ቤቱን የማደራጀት፣ የምዝገባ ቁሳቁስና መዛግብትን አዘጋጅቶ የመጠበቅ፣ ለሕዝቡ ስለምዝገባው ትምህርታዊ ቅስቀሳ የመስጠት ተግባራትንም ያከናውናል።
2. ወሳኝ ኩነቶች መከሰታቸውን በመከታተል ኩነቱ ወደ ተከሰተበት በመሄድ የመመዝገብ (active registration) ስልት
ይህ የአመዘጋገብ ስልት /ዘዴ መዝጋቢው በተመደበበት ቀበሌ ክልል በሚኖሩ ቤተሰቦች መካከል ወሳኝ ኩነቶች መከሰታቸውን በተለያዩ ዘዴዎች (ለምሳሌ፡- በኩነቶች ምዝገባ አስተዳደር ጽ/ቤት ክልል ውስጥ ጠቋሚዎች ወይም አሳዋቂዎችን በማሰማራት) በመከታተልና ኩነቱን የመመዝገብ ሃላፊነት በህግ የተሰጠው አካል በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ኩነቱ ወደ ተከሰተበት በመሄድ ኩነቱንና ተዛማጅ የሥነ-ሕዝብ፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መረጃዎች እንዲመዘግቡ የሚደረግበት የአመዘጋገብ ስልት ነው፡፡
በሀገራችን የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አዋጅ 760/2004 አንቀጽ 14 መሰረት የህዝብ የክብር መዝገብ ከምዝገባ ጽ/ቤት ወጥቶ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የለበት ስለሚል የምንከተለው የምዝገባ ስልት “Passive Registration” ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ አንድ ግለሰብ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የምስክር ወረቀት ቢኖረው ስለሚያገኘው ጥቅም፣ ባለመያዙ ደግሞ የሚያጣው ጥቅም ስለመኖሩ ያለው የግንዛቤ ደረጃ አናሳ ከመሆኑ የተነሳ በምዝገባ ጽ/ቤት ተቀምጦ ተመዝጋቢዎችን ጠብቆ የመመዝገቡ አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ አዳጋች አድርጎታል፡፡ በመሆኑም ህብረተሰቡ በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ጠቀሜታ ላይ ያለው ግንዛቤ አድጎ ኩነቶችን በራስ ተነሳሽነትና በፈቃደኝነት የማስመዝገብ ባህሉ በሚፈለገው ደረጃ ላይ እስከሚደርስ ድረስ በከፍተኛ ሁኔታ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ እና የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የምስክር ወረቀት በሌሎች ተቋማት ያላቸዉን ተፈላጊነት ተግባራዊ በማድረግ የስርዓቱን ቀጣይነትና ውጤታማነት ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው፡፡
ክፍል ሁለት፡- የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አስፈላጊነት እና ጠቀሜታ
2.1. የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አስፈላጊነት
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አስፈላጊነት መሰረታዊና ታሪካዊ መነሻ ግለሰቦች በዜግነታቸው በሀገራቸው ኢኮኖሚ ፣ማህብራዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ሙሉ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን አልፎም በተለያየ ጊዜያት በሀገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደነገጉትን የስብዓዊ፣ የማህበራዊና ፖለቲካዊ መብቶች ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሕጋዊ፣ ግለሰባዊና መንግስታዊ መረጃዎችን ማስገኘት ነው፡፡
የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስርዓት ዓላማ በአንድ ሀገር ውስጥ እና በሌላው የዓለም ክፍል በሚኖሩ የሀገሪቱ ዜጐች ላይ የሚከሰቱ ሁሉንም ወሳኝ ኩነቶች እንደተከሰቱ መመዝገብ ነው፡፡ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ከሕዝብ ቆጠራ ከሚለይባቸው መርሆዎች ውስጥ የምዝገባው የተከታታይነት /Continuity/ መርሆ አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡ይህ መርሆ ከሌላኛው የቋሚነት/permanence/ መርሆ ጋር ተዳምሮ የዜጐችን መብትና ጥቅም ለማረጋገጥ ጉልህ ጠቀሜታ ያላቸውን ግለሰባዊና ህጋዊ መረጃዎችን ማመንጨቱ ከቆጠራና መሰል የስታትስቲክስ መረጃ መሰብሰብ ተግባራት የተለየ ያደርገዋል፡፡ የኩነቶች ምዝገባ መላ ሀገሪቱንና ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል መሸፈኑ፣ በተከታታይነትና በቋሚነት መካሄዱ የወሳኝ ኩነት ስታትስቲክስ መረጃን በማስገኘት ረገድ አግባባዊ የመረጃ ምንጭ እንዲሆን አስችሎታል፡፡
ይሁንና እስከ ቅርብ ጊዜ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አሰራር መርህን የተከተለ ሁሉን አቀፍ፣ ቀጣይ፣ ቋሚና አስገዳጅ የሆነ የወሳኝ ኩነቶች ማለትም ልደት፣ ሞት፣ ጋብቻና ፍቺን የሚመለከት የምዝገባ ሕግም ሆነ ስርአት አልነበረም፡፡ በመሆኑም ሀገሪቷ በዚህ ረገድ የገባቻቸዉን ዓለም አቀፍ ግዴታዎች ከማሟላት አንፃር ክፍተት ፈጥሮ ቆይቷል፡፡ ከዚህም በላይ ህገ-መንግስታዊ ስርአቱን ተከትሎ መንግስት የዘረጋቸው የፌደራልና የክልል አስተዳደሮች የፍትህ፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት አሰጣጥ ስርአትና የየዘርፉን የልማት ዕቅዶችና ፖሊሲዎች ዝግጅትና አፈጻጸም ላይ የበኩሉን አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡ በመሆኑም የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሥርዓትን በሀገራችን መገንባት አስፈላጊ የሆነባቸው ዝርዝር ጉዳዮች ቀጥለን እንመለከታለን፡፡
Ø ዜጐች በሕገ- መንግስቱ እና በሌሎች ሕጐች የተረጋገጠላቸውን መብቶች በአግባቡ እንዲጠቀሙ ለማስቻል
Ø ዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን በተሟላ ሁኔታ እንዲያገኙ ለማድረግ
Ø በሀገሪቱ የሚዘጋጁ የተለያዩ ፖሊሲዎችና ዕቅዶች በተሟላ መረጃ እንዲደገፍ ለማስቻል
Ø በፍትህ አካላት ማስረጃ አቀራረብና ውሳኔ አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ፣
2.2. የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ጠቀሜታ
ከላይ በአስፈላጊነት ካየናቸዉ መሠረታዊ ዕይታዎች አኳያ የምዝገባ ሥርዓቱ ከሚያስገኛቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላሉ፡፡ እነዚህም ህጋዊ፣ አስተዳደራዊ እና ስታትስቲካዊ ጠቀሜታዎች በመባል የሚፈረጁ ሲሆን ከዚህ ቀጥሎ በዝርዝር እንመለከታቸዋለን፡፡
2.2.1. አስተዳደራዊ ጠቀሜታ
2.2.1.1. ለግለሰቦች የሚያስገኘው ጥቅም
ከምዝገባ ስርዓቱ የሚገኙ ህጋዊ የወሳኝ ኩነት ምስክር ወረቀቶች እና በመዝገቦች የሰፈሩ ግለሰባዊ መረጃዎች ግለሰቦች ከመወለድ ጀምሮ በማህበረሰብ አባልነታቸዉ ሊደረግላቸዉ የሚገቡ ህጋዊ እዉቅና ለተሰጧቸዉ መብቶች ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችሏቸዉ ህጋዊ ሰነዶች ናቸዉ፡፡ ከነዚህም ጥቅሞች ዋና ዋናዎቹ በኩነቶች አይነት ከታች ተመልክቷል፡፡
1. የልደት ምዝገባ የሚያስገኘዉ ጥቅም
Ø ስም የማግኘት፡- የግለሰቦች ስም አሰጣጥና የዜጎች ስም በመንግስት ሰነድ የሚያዙበት አሰራር መሰረቱ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስርዓት ነው፡፡ የልደት መዝገብ እና ምስክር ወረቀት የግለሰቦችን ስም በህጋዊ እና በዘለቄታው በመንግስት ሰነድ በማደራጀት ዋነኛ የመረጃ መስረቶች ናቸው፡፡ እነዚህ መረጃዎች ለግለሰቦች ወላጀችንና ቤተሰባዊ ዝምድናን ለማወቅ፣ ስምን ለመቀየር የመረጃ ምንጭ በመሆን ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛሉ፡፡
Ø ዜግነት የማግኘት፡- ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ተከትሎ በህገ-መንግስቱ የዜግነት ድንጋጌዎችን በአግባቡ ለመተግበር የመረጃ መሰረቱና ምንጩ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስርዓት ነው፡፡ ህጻኑ/ኗ ልደታቸው ሲመዘገብ በምዝገባው አዋጅ መሰረት ዜግነት ይሰጣቸዋል፡፡
Ø እድሜ ለማወቅ፡- የሰዎች የትውልድ ቀን እና እድሜ የሰነድ ማረጋገጫ መሰረቱ በአግባቡ የተደራጀ የልደት ምዝገባና ምስክር ወረቀት ነው፡፡
Ø የፓስፖርት ለማግኘት፡- የግለሰቦች የፓስፖርት ሰነድ ዝግጅት ዋናው መሰረት የግለሰቦችን ማንነት የሚያረጋግጥ አስተማማኝ የአስተዳደር መረጃ መኖር ነው፡፡ የግለሰቦች ማንነት በመንግስት ሰነድነት የሚዘጋጅበት አሰራር መሰረቱ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስርዓት ነው፡፡ ይሁን እንጅ በኢትዮጵያ በአግባቡ የተደራጀ የምዝገባ ስርዓት ባለመኖሩ ለፓስፖርት ዝግጅት፣ ቁጥጥርና አስተማማኝነት ትልቅ የመረጃ ክፍተት ሆኖ ቆይቷል፡፡
Ø የማንነት ህጋዊ መሰረትን ለመጣል፡- ወላጆችን ለማወቅ፣ ቤተሰባዊ ዝምድናን ለማወቅ፣ አሳዳጊን ለማቅ፣ ማንነትን ለማወቅ፣ ዜግነትን ለመቀየር፣ ስም ለመቀየር፣
Ø መብትን ለማስጠበቅ፡- የውርስ መብትን ለማስጠበቅ፣ የንብረት ባለቤትነት መብትን ለማግኘት፣ በልጅነት ጊዜ የመጠበቅ መብትን ለመጠቀም፣ ለአካል ጉዳተኛ ህፃናት የኑሮ ድጎማ ለማድረግ፣ የበሽታ መከላከያ መድሃኒቶችን/ክትባቶችን ለማግኘት፣ ከወሊድ በኋላ ህፃናትና እናቶች የጤና እንክብካቤ የማግኘት፣ ወጣት ጥፋተኞች ከእድሜአቸዉ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የህግ ውሳኔና ጥበቃ እንዲያገኙ ለማድረግ፣
Ø ዕድሜን መሠረት በማድረግ የሚሰጡ የአገልግሎት መብቶችን ለመጠየቅ፡- ት/ቤት ለመግባት፣ በስራ ለመሰማራት ፈቃድ ለማግኘት፣ የነዋሪነት ወይም የማንነት መታወቂያ ለመጠየቅ፣ መንጃ ፈቃድ ለማውጣት፣ መሳሪያ የመያዝ ፈቃድ ለማግኘት፣ የውርስ መብት ህጋዊነትን ለማግኘት፣ የመምረጥና መመረጥ መብትን ለመጠቀም፣ ለጋብቻ ብቁነት ፈቃድን ለመጠየቅ፣ የጡረታ ዋስትና ለማግኘት ወይም (ቀድሞ) ጡረታ ለመውጣት (ለመጠየቅ)፣ ...ወዘተ
Ø የትውልድ ቦታን መሰረት በማድረግ የሚገኙ መብቶችን በህጋዊ መረጃ ለማቅረብ፡- ወደ ውጪ ሀገር ለመውጣት ወይም ሀገር ውስጥ የመግባት ፈቃድ ለመጠየቅ፣ ለውጭ ሀገር ጉዞ ፓስፖርት ለመጠየቅ፣ ዜግነትን በህጋዊነት ለመመረት፣ ወደ ሌላ ክልል የመግባት ፈቃድ ለመጠየቅ፣... ወዘተ ያገለግላል።
2. የሞት ምዝገባ ማስረጃ
Ø ለሟች ቀሪ ዘመዶች ሟቹ ለመሞቱ ህጋዊ መረጃ በመሆን፣ ውርስ የሚገባቸው የመውረስ ጥያቄ ለማቅረብ፣ የኢንሹራንስ ጥያቄ ለማቅረብ፣ የቤተሰብ ድጎማ ጥያቄ ለማቅረብ፣ በህይወት ለሚኖረው የትዳር ጓደኛ የማግባት ፈቃድ ለመጠየቅ፣ አጠራጣሪ ወይም የሞቱ ምክንያት ወንጀል ለሆኑ ለሚመለከተው አካል ለመጠቆም ወይም ለማመልከት፣ ሞቱ የተፈጸመበትን ቀንና ቦታ በማሳወቅ ህጋዊ መረጃ በመሆን ለግለሰቦች ከፍተኛ ጠቀሜታ ስገኛል፡፡
3. የጋብቻ ምዝገባ ማስረጃ
Ø ጋብቻ ለመመስረቱ ህጋዊ መረጃ በመሆን፡- ጋብቻው ህጋዊ መሆኑን ለማረጋገጥ፣ የጋብቻዉ ውጤት ለሆኑት ህጻናት በቤተሰብ የመጠበቅ ህጋዊ መብትን ለማረጋገጥ፣ ህጋዊ ወራሽነትን ለማረጋገጥ፣ ከተጋቢዎች አንዳቸው ሲሞቱ ቋሚው የኢንሹራንስ ጥያቄን ለማቅረብ፣ ጋብቻ በሚፈርስበት ጊዜ የልጆች አስተዳደግ ለመወሰን፣ ወደ ውጭ ሀገር ለመጓጓዝ ፓስፖርት የማግኘት ፈቃድን ለማቅረብ፣ የልጆችን ህጋዊነት ለማረጋገጥ፣ የራስን ልጆች ህጋዊነት ለመመስረት እንዲሁም ከሌላ የተወለዱትን ለማስመዝገብ፣ ከገንዘብ ተቋማት ብድር ለመበደር፣ ጋብቻዉ የተፈጸመበትን ቀንና ቦታ በማሳወቅ ህጋዊ መረጃ በመሆን፣ ለግለሰቦች ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡
4. የፍቺ ምዝገባ ማስረጃ
Ø ፍቺ ለመፈፀሙ ህጋዊ ማረጋገጫ በመሆን፡- እንደገና የማግባት ጥያቄን ለማቅረብ፣ ከፍቺ በኋላ የንብረት ክፍፍል ለማድረግ፣ ከፍቺ በኋላ ስለተወለዱ ልጆች ህጋዊ መረጃ ለመሆን፣ ከፍቺ በኋላ በአንደኛቸው የቀድሞ የትዳር ጓደኛ ምክንያት ከሚመጡ የገንዘብ ወይም የንብረት ጥያቄዎች (ዕዳ) ነፃ ለመሆን፣ ፍችዉ ለተፈጸመበት ቀንና ቦታ ህጋዊ መረጃ በመሆን ለማቅረብ ያስችላል፡፡
2.2.1.2. መንግስታዊ ጠቀሜታዎች
የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ መንግስት የሚያወጣቸውን ጥቅል ዕቅዶችና ፕሮግራሞችን መሠረት በማድረግ እስከ ዝቅተኛዉ አስተዳደር ክልል የሚገኘዉን የህብረተሰብ ክፍል አልፎም በቤተሰቦችና በግለሰብ ደረጃ ስለሚሰጡ ልዩ ልዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች ወቅታዊ፣ ቀጣይና ቋሚ ክትትል በማድረግ ፍታዊ እንዲሆኑ የሚያስችል አሠራርና ሥርዓት ለመዘርጋት ጥቅም ላይ የሚውሉ መረጃዎችን በማፍለቅ ጥቅም የሚሰጡበት ነው። ከነዚህም ጥቅሞች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ከታች ተመልክተዋል።
1. ዘመናዊ የማንነት መለያ መረጃ እንዲኖር ያስችላል፡- አገሪቱ ከልማዳዊ አሰራር የተላቀቀ የማንነት መለያ የመረጃ ስርዓት እንዲኖራት ያስችላል:: ለምሳሌ:-
Ø የነዋሪነት መታወቂያ/የፓስፖርት ዝግጅት፡- ወሳኝ ኩነቶቸ ምዝገባ በሀገሪቱ ወጥ የሆነ የመታወቂያ ዝግጀት እና አሰጣት ስርዓት እንዲኖር የመረጃ ምንጭ በመ ያ
Ø የመራጮች መዝገቦችን/ ዝርዝሮችን ለማደራጀት
Ø የግብር ከፋይ መዝገቦችን ለማደስ ያገለግላል'
Ø የቤተሰብ መዝገብ ለማደራጀት፡- ቤተሰብ የመንግስትን ጥበቃ እንዲያገኝ በመንግስት ሰነድነት መደራጀቱ ለበርካታ የእለት ተዕለት የአስተዳደርና ማህበራዊ አገልግሎት ተግባራት ትልቅ እገዛ እንዳለው እሙን ነው፡፡ የቤተሰብ መዝገብን ለማደራጀት የመረጃ መሰረቱ አባላቱን የተመለከቱ በዋነኝነት የልደት፣ የሞት፣ የጋብቻና የፍቺ ምዝገባ መረጃዎች ናቸው፡፡
Ø የአገር ደህንነት መረጃዎች፡- በተቀረው ዓለም እንደሚደረገው ወንጀልን ለመከላከልና ዜጎችን ከጥቃት ለመታደግ የግለሰቦች ማንነትና መሰረታዊ ባህሪያት በተለያዩ የመረጃ ስርአት መያዙ የግድ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ መረጃዎች ለአገር ደህንነት ለሚደራጁ የመረጃ ስርአቶች መሰረት ናቸው፡፡
2. የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ አካላት ለሚሰጡት አገልግሎት ስምሪት ለመስጠት
Ø ከበሽታ ለመከላከልና የጤና እንክብካቤ ለማድረግ
Ø የመሬት ይዞታ አስተዳደርን ለመወሰን
Ø የትራንስፖርት ድርጅቶች እድሜንና ማንነትን ለማወቅ፣
Ø የእርዳታና ድጎማ ለመስጠት (ተረጂዎችን ወይም ተጎጂዎችን ለመለየት)
Ø የስፖርትና መዝናኛ የውድድር ስፖርቶች በተለይ እድሜን በማረጋገጥ ወዘተ
3. የእናቶችንና የህፃናትን ጤና ለማሻሻል
Ø በአንድ የማህበረሰብ ክፍል የተከሰቱ ልደቶችን ከያዘው መዝገብ ዝርዝር በመነሳት ለእያንዳንዷ እናትና ለተወለደው ህፃን ልደቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ተገቢውን የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ የልደት መዝገቡ መነሻ ይሆናል።
Ø ህፃናትን ከታወቁ የልጅነት በሸታዎች ለመከላከል ክትባት ለመስጠት የአካባቢውን የልደት ዝርዝር የሚያሳየው መዝገብ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ በተለይም በመጀመሪያ የተወለዱ ልጆች፣ ሲወለዱ ዝቅተኛ ክብደት ያላቸውን፣ በተለያየ የጤና ቸግር የተነሳ የአካል ጉድለት ወይም ችግር ያለባቸውን እና በወሊድ ወቅት ችግር የነበረባቸውን ለይቶ በቅርበት ለመከታተልና ወቅታዊ ዕርዳታ በመስጠት የአፈፃፀም አቅጣጫ ለማሳየት የመረጃ ምንጭ ከልደት መዝገብ የሚዘጋጀው የልደት ዝርዝር ነው።
Ø ህጻናት ያእድሜአቸው እንዳይዳሩ ለማድረግ ወይም የልጅነት ጋብቻን ለመከላከል ልደት ምዝገባ ወሳኝ ሚና አለው፡፡
4. በህዝብ ጤና አጠባበቅ ፕሮግራም የተላላፊ በሽታዎች ቁጥጥር
Ø በሞት መዝገቡ የሞት ምክንያታቸው በተላላፊ በሽታ በመያዝ ከሆነ ከግለሰቦች መረጃ በመነሳት አፋጣኝ ክትትል በማድረግ በሽታው እንዳይዛመት ከሟቹ ጋር ግንኙነት ያላቸው ቤተሰቦች ተገቢውን ህክምና በወቅቱ እንዲያገኙ ለማድረግ ያስችላል። በዚህ ረገድ እንደ ሳንባ ነቀርሳ፣ የወባ ወረርሽኝ ... ወዘተ በመሳሰሉት ተላላፊ በሽታዎች ተጠቅተው ከሞቱ ሰዎች መረጃ (ከሞት መዝገቡ) በመነሳት ተገቢውን ወቅታዊና ተከታታይ እርምጃዎችን እያንዳንዱን ቤተሰብ መሠረት ባደረገ መልኩ ለመከታተል እና ተላላፊ በሽታዎችን ለመቆጣጠር ከሟች ጋር ግንኙነት ያላቸውን በመለየት አልፎም ለአካባቢው ህብረተሰብ የበሸታውን መከላከያ ክትባት ለመስጠት ዋነኛው የመረጃ ምንጭ የሞት መዝገቡ ነው።
5. ለሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች እና ፕሮግራሞች አፈፃፀም
Ø በህፃናት/ልጆች ጥበቃና እንክብካቤ ተግባር ላይ የተሰማሩ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከተዘጋጀው የልደት መዝገብ በመነሳት የቤተሰብ ድጎማ እና መሰል ማህበራዊ ግልጋሎት ፕሮግራሞችን የአስተዳደር አፈፃፀምና የክትትል ተግባርን ለማከናወን
Ø የጋብቻ ወይም የፍቺ መጠኖችን መሠረት በማድረግ አካባቢያዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በማቋቋም እና በተለይ የጋብቻ ወይም የፍቺ መጠን ከፍተኛ በሆነበት አካባቢ ልዩ ጥናትና ክትትል ለማድረግ፣
Ø የተማሪን ብዛት እና የመምህራን አቅርቦትን
Ø የመኖሪያ ቤቶች ፍላጎት እና የግንባታ ዕቅድን በማዘጋጀት
Ø ልዩ ልዩ የፍጆታ ዕቃዎችን ለማምረትና ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችሉ ዕቅዶችን ለማዘጋጀት ወዘተ የመረጃ ግብዓት በመሆን ያገለግላል፡፡
2.2.2. የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ህጋዊ ጠቀሜታ
1. በፍትሐ-ብሄር ጉዳዮች፡-
Ø ልጅነትን እና ወላጅነትን (በተለይ አባትነትን) በመወሰን፣
Ø መሞትን እና የሞት ምክንያትን በማረጋገጥ፣ የውርስ እና የኢንሹራንስ ጉዳዮችን በመዳኘት፣
Ø የጋብቻ መኖርንና መፍረስን፣
Ø ለአካለ መጠን ስለመድረስ እና የንብረት ባለቤት የመሆን እድሜን በመወሰን
2. በወንጀል ነክ ጉዳዮች
Ø በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን ማንነትና አድራሻ በመለየት እና ወንጀል አድራጊዎችን በትክክለኛ እድሜአቸው መሰረት ቅጣት ለመወሰን የመሳሰሉ የወንጀል ጉዳዮችን በማጣራትና ትክክለኛ ፍትህ ለመስጠ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ መረጃ አስፈላጊ ነው፡፡
2.2.3. ስታትስቲካዊ ጠቀሜታ
1. አገራዊ የሕዝብ ብዛት እና ስርጭት እንዲሁም ለውጥ ክትትል ለማድረግ፡- በሕዝብ ቆጠራ የተገኘን የአንድ ወቅት መረጃ በማደስ አመታዊና ከዚያም ባነሰ የስነ-ህዝብ መረጃዎችን ለማስላት ከወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ በሚገኙ ማለትም የውልደት እና የሞት ልዩነት ወይም የህዝብ ለውጥ (population dynamcis) መከታተያ መረጃዎች ነው፡፡ ግለሰባዊ የስነ-ሕዝብ መረጃዎች በትክክለኛ የማንነት መረጃ ላይ በመመስረት የናሙና እና የሕዝብ ቆጠራ መረጃዎችን ለመሰብሰብ፣ (ስም፣ ቤተሰባዊ ዝምድና፣ ዕድሜ (የትውልድ ቀን)፣ የትውልድ ቦታ፣ … )
የህዝብ ብዛት ስሌት ትክክለኛ የዕድሜና ማንነት መረጃ፣ ከቀበሌ የሚነሳ ዓመታዊ የህዝብ ብዛት መረጃ፣ የትንበያ መረጃ ዝግጅት (projection)፣ ልዩ አገልግሎት የሚፈልጉ ሰዎች ብዛት በተናጥል ዕድሜ (ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ብዛት በተናጥል ዕድሜ፣ በትምህርት ዕድሜ ክልል ያሉ ልጆች ብዛት በተናጥል ዕድሜ፣ …)፣ የህዝብ ብዛት ዕድገት ስሌት፣ የዕድገት መለኪያዎች ስሌት (development indicators)፣ የልደት ምጥነት፣ የህጻናት ሞት ምጥነት፣ የእናቶች ሞት ምጥነት፣ የሴት ልጆች የትምህርት ተሳትፎ፣ የህይወት ዘመን ስሌት (Life Expectancy)፣ የሞት ምክንያት በበሽታዎች ዓይነትና የስነ-ሕዝብ አደረጃጀት ለበርካታ የኢኮኖሚና ማህበራዊ የምጥነት መለኪያዎች የማካፈያ (Denominator) መረጃ በማቅረብ - including GDP per Capita,
Demographic Equation
Pt+1= Pt + Bt to t+1 - Dt to t+1 + It to t+1 - Et to t+1
Where፡- t= a given year
Pt+1 = population size at time t+1
Pt= population size at time t
Bt to t+1= the number of births occur b/n t and t+1
Dt to t+1= the number of deaths occur b/n t and t+1
It to t+1= the number of immigrants occur b/n t and t+1
Et to t+1= the number of emigrants occur b/n t and t+1
Bt to t+1 - Dt to t+1= natural population increase
It to t+1 - Et to t+1= net migration
2. በጥናትና በምርምር ተግባር
በዚህ ዘርፍ ወሳኝ ኩነቶች ስታትስቲክስ በሁለት ዋና ዋና መስኮች የጥናትና የምርምር ተግባር ጥቅም ላይ ይውላል።
Ø በስነ-ሕዝብ ስታቲስቲክስ ጥናትና ምርምር (Demographic Study and Research) በስነ-ሕዝብ የምርምር ተግባር ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት የሕዝብ ብዛት ግምት (population estimation)፣ የሕዝብ ብዛት ትንበያና (population projection) እና የስነ-ሕዝብ ትንተና ጥናቶች (population analytical studies) ናቸው። እነዚህ የመረጃ አቅርቦትና የትንተና ሥራዎች በዝቅተኛ የአስተዳደር ዕርከን ደረጃ በቀጣይነትና በቋሚነት ሊቀርቡ የሚችሉት ቀጣይና ቋሚ የወሳኝ ኩነት ስታቲስቲክስ መረጃዎች በሕዝብ የክብር መዝገብ የመረጃ ምንጭ አማካይነት ነው።
Ø በህክምና ምርምር ዘርፍ (medical Research)፡- ይኽ የምርምር ዘርፍ የወሳኝ ኩነቶች ስታትስቲክስ በስነ-ሕዝብ የምርምር መስክ ከሚያስገኘው አገልግሎት ጋር በተያያዘ በህክምናው ዘርፍ የህክምና ባለሙያዎች ምርምር የሚያካሂዱበት የሥራ መስክ ነው። በዚህ የምርምር መስክ የወሳኝ ኩነት ስታቲስቲክስ መረጃዎችን በግብዓትነት በመጠቀም በርካታ የህክምና ውጤቶች በጤናው ዘርፍ ተበርክተዋል።
ክፍል ሦስት፡- የወሳኝ ኩነቶች አስመዝጋቢ አካላት እና ደጋፊ ማስረጃዎች
3.1. የወሳኝ ኩነቶች አስመዝጋቢ አካላት
በአገሪቱ የተዘረጋዉን የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስርዓት ወጥና ጥራት እንዲኖረዉ በማድረግ ከምዝገባዉ የሚገኙ መረጃዎችን ለህግ፣ ለአስተዳደር እና ለስታትስቲክስ አገልግሎት ግብአት ሆኖ እንዲያገለግል ለማድረግ የኢምግሬሽ ዜግነት አና ወሳኘኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ በወሳኝ ኩነት ምዝገባና የብሄራዊ መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 760/2004 አንቀጽ 70(2) በተሰጠዉ ስልጣን መሰረት የእያንዳንዱን ኩነት አመዘጋገብ፣ የኩነቶችን አስመዝጋቢዎች በተመለከተ እና ከአስመዝጋቢዎች ወይም ከተመዝጋቢዎች የሚጠበቁ ቅድመ ሁኔታዎች እና ደጋፊ ማስረጃዎች በዝርዝር የያዘ መመሪያ አውጥቷል፡፡ በዚህ መመሪያ መሰረት የእያንዳንዱን ኩነት አስመዝጋቢ ስናይ
1. የልደት አስመዝጋቢ
· የህፃኑ ወላጆች በህይወት ካሉ አባት እና እናት ሁለቱም ወይም ልደትን ለማስመዝገብ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ተገኝቶ ልደቱን ማስመዝገብ ያልቻለው ወላጅ አባት ከሆነ ለህፃኑ ወላጅ እናት ልዩ የልደት ውክልና በመስጠት እንዲሁም ተገኝታ ማስመዝገብ ያልቻለችው ወላጅ እናት ከሆነች ለህፃኑ ወላጅ አባት ልዩ የልደት ውክልና በመሰጠት ልደትን ማስመዝገብ ይቻላሉ፡፡
· ከወላጆቹ አንዱ በህይወት የሌለ እንደሆነ በህይወት ያለው ወላጅ የሟች ወላጅንህጋዊ የሞት ማስረጃ ሲያቀርብ ልደቱ ይመዘገባል፡፡
· ችሎታ የሌላቸው ሰዎች በተንከባካቢዎቻቸው ወይም በአሳዳሪዎቻቸው አማካይነት መመዝገብ ይችላሉ፡፡
· ዕድሜው 18 ዓመትና በላይ የሆነ ልደት ምዝገባ አገልግሎት ፈላጊ ልደቱን ራሱ ማስመዝገብ አለበት፡፡
· 18 ዓመት ሳይሞላቸው ልጅ የወለዱ ወላጆች ከሚኖሩበት መደበኛ መኖሪያ ቦታ ካለው ዝቅተኛ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ማንነታቸውን የሚገልጽ የድጋፍ ደብዳቤ በማቅረብ የልጃቸውን ልደት ማስመዝገብ ይችላሉ፡፡
· ተጥሎ የተገኘ ህጻን ከሆነ ፖሊስ ወይም አግባብ ያለዉ አካል ያስመዘግባል፡፡
2. የጋብቻ አስመዝጋቢ
· ጋብቻው የተፈፀመው በክብር መዝገብ ሹም ፊት ከሆነ የክብር መዝገብ ሹሙ ጋብቻውን ወዲያውኑ መመዝገብ አለበት፡፡
· ጋብቻው በሃይማኖታዊ ወይም በባህላዊ ስርዓት የተፈፀመ እንደሆነ ተጋቢዎቹ ጋብቻውን ማስመዝገብ አለባቸው፡፡
3. የፍቺ አስመዝጋቢ
· ተፋቺዎች በጋራ ወይም ከተፋቺዎቹ አንዱ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት የተወሰነ የፍቺ ውሳኔን ለክብር መዝገብ ሹም በማቅረብ ፍቺውን ማስመዝገብ አለባቸው፡፡
4. የሞት አስመዝጋቢ
· ከሟች ጋር አብሮ ይኖር የነበረ ሰው ሟች መሞቱን ማስመዝገብ አለበት፡፡
· ከሟች ጋር አብሮ ይኖር የነበረ ሰው የሌለ እንደሆነ የሟች የስጋ ወይም የጋብቻ ዘመዶች፣ እነዚህ የሌሉ እንደሆነ የቅርብ ጎረቤት ወይም ስለሟቹ መሞት የሚያውቅ ማንኛውም ሰው ሟች መሞቱን ማስመዝገብ አለበት፡፡
· በአደጋ ወይም ባልታወቀ ምክንያት ሞቶ ማንነቱ ስላልታወቀ አስክሬን ሪፖርት የተቀበለ ፖሊስ ሪፖርቱ ከደረሰው ቀን በኋላ ባሉት ሦስት ቀናት ውስጥ ሞቱን ማስመዝገብ አለበት፡፡
· የመከላከያ ሠራዊት አባል በግዳጅ ላይ እያለ ከሞተ የክፍሉ አዛዥ በአገር መከላከያ ሚኒስቴር እንደ ክብር መዝገብ ሹም እንዲሠራ ለተመደበው ኃላፊ ሞቱን በማሳወቅ ማስመዝገብ አለበት፡፡
· ሞቱ የተከሰተው በአዳሪ ትምህርት ቤት ወይም በሌላ የጋራ መኖሪያ ስፍራ የሆነ እንደሆነ የተቋሙ ሃላፊ ሞቱን ማስመዝገብ አለበት፡፡
· ሞቱ የተከሰተው በማረሚያ ቤት ውስጥ የሆነ እንደሆነ ወይም የሞት ቅጣት ፍርድ የተፈጸመ እንደሆነ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ሞቱን ማስመዝገብ አለበት፡፡
3.2. ኩነቶችን ለማስመዝገብ የሚያስፈልጉ ማስረጃዎች
1. ልደትን ለማስመዝገብ ከአስመዝጋቢ/ከተመዝገቢ የሚጠበቁ ማስረጃዎች
· ልደትን ለማስመዝገብ አስመዝጋቢ ወይም ተመዝጋቢ ጊዜው ያላለፈበት የነዋሪነት ወይም ብሔራዊ መታወቂያ ወይም ከዝቅተኛው የአስተዳደር ጽህፈት ቤት መደበኛ ነዋሪነቱን የሚገልጽ የድጋፍ ደብዳቤ ወይም ስደተኛነቱን የሚገልጽ ማስረጃ ወይም የመኖሪያ ፍቃድ ወይም ከሚሰራበት መስሪያ ቤት ባልደረባነቱን እና ዜግነቱን የሚገልጽ የድጋፍ ደብዳቤና የመስሪያ ቤቱን መታወቂያ ወይም የመከላከያ ሰራዊት መታወቂያ ማቅረብ አለበት፣
· ካምፕ/ፕሮጀክት በሚገኝበት አስተዳደር ጽ/ቤት (የምዝገባ ጣቢያ) መደበኛ ነዋሪነት መታወቂያ የሌላቸዉ ልደት አስመዝጋቢወችና ተመዝጋቢወች ልደትን ማስመዝገብ ሲፈልጉ ካምፑ /ፕሮጀክቱ /ፋብሪካዉ የምዝገባ ጽ/ቤቱ በሚገኝበት አስተዳደር ጽ/ቤት አካባቢ መሆኑን በማረጋገጥና ተመዝጋቢወቹ /አስመዝጋቢወቹ የካምፑ/የፕሮጀክቱ/የፋብሪካዉ ሰራተኛ መሆናቸዉን የሚገልጽ ማስረጃ ሲያቀርቡ መመዝገብ ይችላሉ፣
· ልደቱ የተከሰተው በጤና ተቋም ከሆነ አስመዝጋቢው ከጤና ተቋም የተሰጠውን የልደት ማሳወቂያ ምስክር ወረቀት ማቅረብ አለበት፣
· የህጻኑ አሳዳሪ ወይም ተንከባካቢ ልደቱን ለማስመዝገብ ሲቀርብ ከፍርድ ቤት የተሰጠ ሕጋዊ ማስረጃ ማቅረብ አለባቸው፣
· ተጥሎ የተገኘ ህፃን ለማስመዝገብ የሚመጣ ፖሊስ ወይም አግባብ ያለው የመንግስት አካል ማንነቱን የሚገልጽ ሕጋዊ መታወቂያ ወይም ማስረጃ ማቅረብ አለበት፣
· ልደት ተመዝጋቢው የውጭ ዜጋ ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደ መሆን አለበት፣
· ዘግይተውና የምዝገባ ጊዜውን አሳልፈው ለሚቀርቡ ተመዝጋቢዎች በእስር ላይ የቆዩ ከማረሚያ ቤት ማስረጃ፣ በህክምና ላይ ከቆዩ ከጤና ተቋሙ የህክምና ማስረጀ፣ በእምነት ተቋማት በህክምና ሲረዱ የቆዩ ከእምነት ተቋሙ ማስረጃ እና በባህላዊ ህክምና ሲረዱ ከቆዩ ባህላዊ ህክምናውን ካገኙበት አካል ማስረጃ ማቅረብ አለባቸው፡፡
2. ጋብቻን ለማስመዝገብ ከአስመዝጋቢ የሚጠበቁ ነገሮች
· ሁለቱ ተጋቢዎች ጊዜዉ ያላለፈበት የነዋሪነት ወይም ብሔራዊ መታወቂያ ወይም ከዝቅተኛው የአስተዳደር ጽህፈት ቤት መደበኛ ነዋሪነቱን የሚገልጽ የድጋፍ ደብዳቤ ወይም ስደተኛነቱን የሚገልጽ ማስረጃ ወይም የመኖሪያ ፍቃድ ወይም ከሚሰራበት መስሪያ ቤት ባልደረባነቱን እና ዜግነቱን የሚገልጽ የድጋፍ ደብዳቤና የመስሪያ ቤቱን መታወቂያ ወይም የመከላከያ ሰራዊት መታወቂያ ማቅረብ አለበት፣
· ካምፕ/ፕሮጀክት በሚገኝበት አስተዳደር ጽ/ቤት መደበኛ ነዋሪነት መታወቂያ የሌላቸዉ ጋብቻ አስመዝጋቢዎችና ተመዝጋቢዎች ጋብቻን ማስመዝገብ ሲፈልጉ ካምፑ/ፕሮጀክቱ/ፋብሪካዉ የምዝገባ ጽ/ቤቱ በሚገኝበት አስተዳደር ጽ/ቤት አካባቢ መሆኑን በማረጋገጥ ተመዝጋቢዎቹ/አስመዝጋቢዎቹ የካምፑ /የፕሮጀክቱ /የፋብሪካዉ ሰራተኛ መሆናቸዉን የሚገልጽ ማስረጃ ሲያቀርቡ መመዝገብ ይችላሉ፣
· በሙሽራው በኩል ሁለት በሙሽሪት በኩል ሁለት በድምሩ አራት ምስክሮች አገልግሎቱ ያላለፈበት የነዋሪነት/ብሄራዊ ወይም ፓስፖርት ወይም የመከላከያ ሰራዊት መታወቂያ ወይም ማንነታቸውን የሚገልጽ ማስረጃ መቅረብ አለበት፣
· ሙሽራው/ዋ ከዚህ በፊት አግብቶ/ታ የፈታ/ች ከሆነ የፍች ምስክር ወረቀት መቅረብ አለበት፣
· ከ6 ወር ወዲህ በተመሳሳይ ጊዜ የተነሱት ሁለት ሁለት 3 በ 4 የሆነ የተጋቢዎች ፎቶ ግራፍ ማቅረብ አለባቸዉ፣
· በሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ስርዓት የተፈፀመ ጋብቻ የተጋቢዎች ምስክሮች ወይም በጋብቻ ስርዓቱ ላይ የታደመ ሰዉ በክብር መዝገቡ ሹም ፊት በአካል ቀርበዉ ፊርማቸዉን ማኖር አለባቸዉ፣
· ዘግይተውና የምዝገባ ጊዜውን አሳልፈው ለሚቀርቡ ተመዝጋቢዎች የዘገዩበትን ምክንያት ማስረጃ ማቅረብ አለባቸው፡፡
3. የሞት ኩነትን ለማስመዝገብ ከአስመዝጋቢ የሚጠበቅ
· ሞቱ የተከሰተው በጤና ተቋም ከሆነ ከጤና ተቋም የተሰጠ ማስረጃ መቅረብ አለበት፣
· አስመዝጋቢዉ ጊዜው ያላለፈበት የነዋሪነት ወይም ብሔራዊ መታወቂያ ወይም ከዝቅተኛው የአስተዳደር ጽህፈት ቤት መደበኛ ነዋሪነቱን የሚገልጽ የድጋፍ ደብዳቤ ወይም ስደተኛነቱን የሚገልጽ ማስረጃ ወይም የመኖሪያ ፍቃድ ወይም ከሚሰራበት መስሪያ ቤት ባልደረባነቱን እና ዜግነቱን የሚገልጽ የድጋፍ ደብዳቤና የመስሪያ ቤቱን መታወቂያ ወይም የመከላከያ ሰራዊት መታወቂያ ማቅረብ አለበት፡
· ሞቱ የሚመዘገበው በግለሰቡ መጥፋት ውሳኔ ምክንያት ከሆነ የፍርድ ቤት ውሳኔ ትክክለኛ ቅጂ መቅረብ አለበት፣
· የጊዜ ገደቡ ባለፈ ምዝገባ ለሚመዘገብ ሞት ስለ ሞቱ መከሰት የሚገልጽ የተረጋገጠ የጽሁፍ ማስረጃ መቅረብ አለበት፡፡ ማስረጃዉ የሚቀርበዉ ከእድር፣ ከቤተክርስቲያን፣ ከመስጅድና ከመሳሰሉት ይሆናል፣
· ሞቱ የተከሰተው በውጭ አገር ዜጋ ላይ ከሆነ ከጤና ተቋም የተሰጠ የሞት ማሳወቂያ ወረቀት ወይም ከእድር፣ ከቤተክርስቲያን፣ ከመስጅድና ከመሳሰሉት መቅረብ አለበት፣
· ዘግይተዉና የምዝገባ ጊዜዉን አሳልፈዉ ለሚቀርቡ ተመዝጋቢዎች በእስር ወይም በህመም ወይም በመሳሰሉት የቆዩ ከሆነ ከሚመለከተዉ አካል ማስረጃ ማቅረብ አለባቸዉ፣
4. የፍች ኩነትን ለማስመዝገብ ከአስመዝጋቢ የሚጠበቅ
· ፍቺው በፍርድ ቤት የተከናወነ መሆኑን የሚገልፅ የፍርድ ቤት ውሳኔ ግልባጭ መቅረብ አለበት፡፡
· አስመዝጋቢ ወይም ተመዝጋቢ ጊዜው ያላለፈበት የነዋሪነት ወይም ብሔራዊ መታወቂያ ወይም ከዝቅተኛው የአስተዳደር ጽህፈት ቤት መደበኛ ነዋሪነቱን የሚገልጽ የድጋፍ ደብዳቤ ወይም ስደተኛነቱን የሚገልጽ ማስረጃ ወይም የመኖሪያ ፍቃድ ወይም ከሚሰራበት መስሪያ ቤት ባልደረባነቱን እና ዜግነቱን የሚገልጽ የድጋፍ ደብዳቤና የመስሪያ ቤቱን መታወቂያ ወይም የመከላከያ ሰራዊት መታወቂያ ማቅረብ አለበት፣
· ካምፕ/ፕሮጀክት በሚገኝበት አስተዳደር ጽ/ቤት መደበኛ ነዋሪነት መታወቂያ የሌላቸዉ ፍች አስመዝጋቢወችና ተመዝጋቢወች ፍች ማስመዝገብ ሲፈልጉ ካምፑ /ፕሮጀክቱ /ፋብሪካዉ የምዝገባ ጽ/ቤቱ በሚገኝበት አስተዳደር ጽ/ቤት አካባቢ መሆኑን በማረጋገጥና ተመዝጋቢወቹ /አስመዝጋቢወቹ የካምፑ/የፕሮጀክቱ/የፋብሪካዉ ሰራተኛ መሆናቸዉን የሚገልጽ ማስረጃ ሲያቀርቡ መመዝገብ ይችላሉ፣
· ፍቺው የሚመዘገበው በህጋዊ ወኪል ከሆነ ህጋዊ ወኪሉ የውክልና ማስረጃ ማቅረብ ይኖርበታል፣
· ዘግይተውና የምዝገባ ጊዜውን አሳልፈው ለሚቀርቡ ተመዝጋቢዎች በእስር ወይም በህመም ወይም በመሳሰሉት የቆዩ ከሆነ ከሚመለከተዉ አካል ማስረጃ ማቅረብ አለባቸዉ፡፡
የመረጃ ምንጮች
1.የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ.በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስርዓት ግንባታ የከፍተኛ አመራር
ማሰልጠኛ ሞጁል (ረቂቅ) መስከረም 2ዐዐ8 ዓ.ም አዲስ አበባ
2. ለክልል ወሳኝ ኩነት መዝጋቢ ተቋማት የተዘጋጀ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 7/2010
3. የየማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ /2ዐዐ2 ዓ.ም (የወሳኝ ኩነቶች) ልደት፣ ሞት፣ ጋብቻና ፍቺ /ምዝገባና ስታትስቲክስ አዲስ አበባ፣
4. የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወከዮች ምክር ቤት (2ዐዐ4 ዓ.ም) በአዋጅ ቁጥር 76ዐ/2ዐዐ4 የወጣው የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ እና የብሄራዊ መታወቂያ አዋጅ፣
5. በኢፌዲሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት (2ዐዐ5 ዓ.ም) በደንብ ቁጥር 278/2ዐዐ5 የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ ለማቋቋም የወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ፣
6.የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግስት የፍታሃብሄር ሕግ (1952 ዓ.ም) አዲስ አበባ
7.በፍትህና ሕግ ስርዓት ኢኒስቲትዩት የፍትሕ ስርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም /2ዐዐዐዓ.ም/ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ረቂቅ ህግን ለማዘጋጀት የቀረበ ጥናታዊ የጽሑፍ ሪፖርት፣
8.የኢፌዲሪ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ/2ዐዐ8 ዓ.ም የወሳኝ ኩነት ምዝገባ መሪ መመሪያ ረቂቅ /ለውይይት የቀረበ/
9.United Nations (2014). Principals and Recommendation For a Vital Statistics System. /Revision 3/ United Nations. New York፣
10. United Nations Economic Commission for Afrrica (2012). Africa Programme on Accelerated Improvement of Civil Registration and Vital Statistics (APAI CRVS), Durban, South Africa.
11. United Nations (2002). Handbook on Training in Civil Registration and Vital Statistics Systems , Series F,no .84 /New York